የብቃት ማረጋገጫ ፈተናን ከወሰዱ መምህራን ማለፍ ያቻሉት 19 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው

(EBC)- በአዲስ አበባ ከተማ የብቃት ማረጋገጫ ለማግኘት የፅሁፍ ፈተና ከወሰዱ 5 ሺህ 167 የመጀመሪያ ደረጃ መምህራን ውስጥ 9 መቶ 61ዱ መምህራን ብቻ ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ መቻላቸውን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ገለጸ፡፡

ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2008 ዓ.ም በተከታታይ በየአመቱ በተሰጠው የብቃት ማረጋገጫ የፅሁፍ ፈተና 18 ነጥብ 8 በመቶ መምህራን ብቻ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፋቸውን በትምህርት ቢሮ የሞያ ፍቃድ አሰጣጥና እድሳት ዳይሬክቶሬት ዳይሪክተር አቶ አስማማው እስተዚያ ለኢቢሲ ተናግረዋል፡፡

በከተማዋ በአጠቃላይ ወደ 11 ሺህ ገደማ የመጀመሪያ ደረጃ መምህራን ያሉ ሲሆን እስካሁን የምዘና ፈተናውን የወሰዱት ግማሽ ያህሉ ብቻ መሆናቸውን አቶ አስማማው ገልጸዋል፡፡

የብቃት ማረጋገጫ ምዘናው 80 በመቶ የሚሆነውን የሚይዘው የፅሁፍ ፈተናው መሆኑና ቀሪውን 20 በመቶ የማህደር ተግባር ምዘና የሚሸፈን መሆኑ ተገልጿል፡፡

የመምህራኑ የምዘና ውጤት መምህራኑ ከሚያገኙት ትምህርትና ከስልጠና ጀምሮ በፈተና ሂደቱ ውስጥም ያለውን ክፍተት እንደሚያሳይ ፤ነገር ግን እንደጅምር ከሌሎች አገራት ተሞክሮም አንፃር በጊዜ ሂደት የሚሻሻልና ጥሩ የሚባል እንደሆነ አቶ አስማማው ገልፀዋል፡፡

የብቃት ምዘና ፈተናው መሰጠቱ መምህራኑ በአጠቃላይ በመማር ማስተማር ሂደቱ የሚገኙበትን አቋም ለማሳወቅ የሚያስችልና ያለባቸውን ክፍተትም በመጠቆም ተገቢ ስልጠና ለማግኘት ያስችላል ተብሏል፡፡

የህዳሴ መጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የሂሳብ መምህር የሆኑት አቶ ኃይለጊዮርጊስ ሙሉነህ ፈተናው የመምህሩን ሁለገብ ብቃት በሚገባ የሚፈትን እንደሆነና እሳቸውም ውጤቱን እንደጠበቁት ባይሆንም ከትምህርት ቤቱ ያለፉ ብቻኛ መምህር መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

የሞያ ብቃት ማረጋገጫ ምዘና በአንድ ጊዜ ሁሉንም መምህራን ለመመዘን ከአቅም አንፃር  አዳጋች እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን በሂደት ግን ሁሉንም መምህራን በመመዘን የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት እንደሚሰጣቸው ተገልጿል፡፡

Leave A Reply

Your email address will not be published.