የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብታዊ እድገት ከኬንያ በልጧል

(ኢዜአ)- ኢትዮዽያ የልማት ፕሮጀክቶቿ ኢንቨስትመንትን በማሳደግ ላይ እንዲያተኩሩ በማድረጓ በምጣኔ ሃብታዊ እድገት የመሪነት ደረጃውን ከኬንያ እንድትረከብ ማድረጉን የኬንያው ስታንዳርድ ዲጂታል በድረ ገጹ አስነብቧል።

ዘገባው በአፍሪካ የኮንስትራክሽን አዝማሚያ ላይ ክትትል በማድረግ ሪፖርት የሚያወጣውን ዴሎይት የተሰኘ ተቋም የ2017 ሪፖርት ዋቢ አድርጎ ነው ይህን ያለው::

 ኢትዮዽያ ለእያንዳንዱ ኢንቨስትመንት ከምትመድበው በጀት ውስጥ 40 በመቶውን ለቁልፍ የልማት ፕሮጀክቶች ስታውል፥ ኬንያ ግን 20 በመቶውን ብቻ እንደምትመድብ ተጠቅሷል።

እኤአ በ2016 በአካባቢው ግዙፍና ፈጣን ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት ያስመዘገበችው ኢትዮዽያ በምጣኔ ሃብታዊ እድገቷ አሁንም ከኬንያ ቀዳሚ ሆና እንደምትቀጥል ዘገባው አመላክቷል።

ኬንያ በ2016 እና 2017 መካከል በርካታ የልማት ፕሮጀክቶች የነበሯት ቢሆንም፥ በተጠቀሱት ዓመታት በኢትዮዽያ እየተካሄዱ የነበሩ ፕሮጀክቶች ከኬንያ በእጥፍ እንደሚበልጡ የዴሎይት ሪፖርት አሳይቷል።

በተጠቀሱት ጊዜያት በኬንያ እየተካሄዱ ከነበሩት የልማት ፕሮጀክቶች ውስጥ የትራንስፖርት ዘርፉ 53 በመቶ ሲይዝ የማዕድን ዘርፉ 23 በመቶ፣ ሪል ስቴት 14 በመቶ እንዲሁም የውሃ ፕሮጀክቶች ደግሞ ስድስት በመቶ መያዛቸውን ነው መረጃው ያመላከተው።

ኢትዮዽያ በአሁኑ ወቅት በቢሊዮኖች በሚቆጠር ዶላር  ታላቁ የህዳሴ ግድብን እና የኮይሻ የውሃ ሃይል ማመንጫን እውን ለማድረግ እየሰራች መሆኗም ተጠቅሷል።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) ባወጣው ሪፖርት የኢትዮዽያ ኢኮኖሚ በሃገር ውስጥ ጥቅል ምርት(GDP) ጭምር ከኬንያ እንደሚበልጥ አመላክቷል።

በአጠቃላይ ዓመታዊ የዕቃዎችና የአገልግሎት ዘርፍ ዕድገት ኢትዮጵያ 73 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ስታስመዘግብ፥ ኬንያ ግን ያስመዘገበችው 69 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን አሳይቷል።

በአፍሪካ የዴይሎቴ የመሰረተ ልማትና ካፒታል ፕሮጀክቶች ሃላፊ ዢያን ፒየር ላበስካግኔ “በእውነት ኢትዮዽያውያን መልካም ስራ እየሰሩ ነው፤ በአንፃራዊነት በአጭር ጊዜ ውስጥ ከምንም ተነስተው አሁን ያሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል።” ሲሉ መናገራቸውን የስታንዳርድ ዘገባ ያሳያል።

Comments (0)
Add Comment