UPDATE on Sheikh Mohamed

(www.EthiopiaFirst.com) – ሼህ ሙሓመድ ሁሴን አሊ አላሙዲን አሁንም ድረስ Ritz-Carlton ሆቴል የሚገኙ ሲሆን ጤንነታቸው ምንም እንከን የሌለበትና በእጅጉ ደህና መሆናቸውን ከቤተሰብ አባላቶቻቸው ለመስማት ችለናል።

እንደ ምንጮቻችን ምስክርነት ሼህ ሙሓመድ ከቤተሰባቸው ጋር የስልክ ግኑኝነት እያደረጉ ይገኛል።

“የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ” በሚል ሀገሬው የሚጠራቸው ሼህ ሙሓመድ፤ ለህዝባቸውና ለሀገራቸው ሁሌም ፈጥኖ ደራሽነታቸውን ያስመሰከሩ ናቸው።

ሀገር በሻእዕቢያ ተወራ የውጭ ምንዛሪ በጠፋበት ወቅት በኢትዮጵያዊነታቸው የማይደራደሩት የችግር ቀን ደራሹ ለእማማ ኢትዮጵያ ፈጥነው የደረሱ ነበሩ፤

ሀገራችን የ2ሺኛ ዓመት ልደቷን ስታከብር፤ “ለኢትዮጵያ ያልሆነ ይበጣጠስ” ብለው ድምቅ ያለ ዝግጅት እንዲከበር አስተዋፅዋቸው ልዩ ነበር፤

የአፍሪካ ህብረትን ከኢትዮጵያ ነቅሎ ለመውሰድ ዘመኑን በሙሉ ሲዳክር የኖረው የሊብያው ጋዳፊ “ኢትዮጵያ ውስጥ የምንንቀሳቀስበት መኪና እንኩዋን የለም” ብሎ ሲሳለቅ፤ በውዷ ሀገሬማ ማንም አይዘባበትባትም ያሉት ሼህ ሙሓመድ ወድያውኑ ከጀርመን የመርሰዲስ መዓት በአውሮፕላኖች አሰልፈው በማምጣት የህዝብ ኩራትነታቸውን በተግባር ያሳዩ ናቸው፤

በሃገራችን አንድ እንኩዋን የልብ ህክምና ማዕከል በሌለበት ወቅት እዚህ ሀገር ላይ የልብ ህመም ማለት የሞት ፍርድ ማለት ነበር። ይህንን አሳዛኝ እውነታ የሰሙት ሼህ ሙሓመድ በአስር ሚልዮኖች የሚቆጠር ገንዘባቸውን አፍስሰው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ State-of-the-Art የሆነ የልብ ህሙማን ማዕከል አስገንብተዋል፤

የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነት በመነሳት “አይበገሬ” ተብሎ ሲነገርለት የኖረው የአባይ ወንዝን ለመገደብ ሲነሳ፤ “ከሀገር በላይ ምን አለ?” በማለት በአንድ ቼክ 1.5 ቢልዮን ብር ያቀረቡ ናቸው፤

“ቆሼ” ተንዶ ህዝባችንን ሲጨርስ በጉዳቱ ለተጠቁት ቤተሰቦች አርባ ሚልዮን ብር ገደማ ብር ለመስጠት ስስት አልታየባቸውም፤

አምና ሰማዩ ዘግቶ ድርቅ ሲከሰት ህዝባችንን ከሞት ለመታደግ በአስር ሚልዮኖች ብር የሚገመት እህል በመግዛት ድርቁ ወደባሰባቸው የኢትዮ-ሱማሌ ክልልና ቦረና አካባቢ እንዲደርስ አድርገዋል፤

ብዙ ትምህርት ቤት ያሉ ህፃናት በቤታቸው የሚበሉት ምግብ ስለሌለ ትምህርት ላይ እያሉ ይወድቃሉ የሚል አሳዛኝ ጉዳይ የሰሙት ሼህ፤ ልጆች እኮ የአምላክ ስጦታ ናቸው በማለት በየአመቱ አርባ ሚልዮን ብር እየደጎሙ ጠኔ የሚያሰቃያቸው ወገኖቻችንን እየመገቡ ይገኛሉ፤

በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ልጆች ይኖሩበት ከነበረው ከክልል ሱማሊያ በግፍ ተፈናቅለው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ መባልን ሲሰሙ ለአንዳንድ ነገሮች ለማገዝ እንዲረዳ በማለት አርባ ሚልዮን ብር ለግሰዋል፤ (አለመታደል ሆኖ ሼሁ በአሁኑ ወቅት ሪያድ ውስጥ ታግተው ተቀመጡ እንጂ እንደ እቅዳቸው ቢሆን ኖሮ በአካል ተገኝተው ሊያፅናኗቸው ቀጠሮ ቆርጠው ነበር)

ሼህ ሙሓመድ “ጣና ታሟል፤ እንቦጭ ወሮታል” ሲባሉ የገንዘብ መጠኑ ምንም ይሁን ምን እንቦጭን ድራሹን የሚያጠፋ ማሽን የት እንደሚገኝ ጠቁሙኝና ገዝቼ አስመጣለው በማለት ቃል ገብተዋል። ሳዑዲ ሆቴል ውስጥ ታግተው እስከቀሩበት ወቅት ድረስ ማሽኑን የሚያመርቱትን ድርጅቶች እያፈላለጉ እንደነበር ይታወሳል፤

እንዲህ … እንዲህ እያልን ብዙ መመስከር ይቻላል።

እንግዲህ እንዲህ ያሉት የሀገር ጌጥና ክብርን ነው ሰሞኑን አንዳንዶች ፌስቡክ ላይ ፍፁም ውሸት የሆነ ዜና በመፈብረክ “ሼሁ ተገረፉ፤ ሼሁ ታመሙ … ” በማለት ሲፅፉ የምናየው። እውን ይህኝን ለመሰሉ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ ይህንን ማለት አያስተዛዝብም?? ሌላው ቢቀር ጠኔ አየበረታባቸው በየትምህርት ቤቱ ለሚወድቁት የድሃ ልጆች ሲባል እንኩዋን ለይኚ ደግ ኢትዮጵያዊ ሰው ክፉ ይመኛል??

እውነተኛ ኢትዮጵያዊ ይህንን አይነት ክፋት እንደማይመኝ ሁላችንም እናውቃለን። ይህኚን የድሃ አባት የኢትዮጵያ አምላክ ከክፉ ይጠብቃቸው!!

Leave A Reply

Your email address will not be published.